Saturday, December 22, 2012

Home


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ክቡራን አንባብያን ቅኔና አመጣጡን በሚቀጥሉት ቀናት  እንገልፃለን። ይህም የሆነበት ምክንያት ከጊዜ  እጥረት የተነሳ  መሆኑን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።
አሁን ግን  ወቅታዊ በሆኑት ነገሮች ላይ የተዘጋጁትን ቅኔያት እናስነብባችኋለን። እነዚህንም  ቅኔያት በተመለከተ ለሚነሱ አስተያየትና ጥያቄ  የድረ ገጹ ባለቤት በደስታ  ይቀበላሉ።

1.ጉባኤ ቃና :-

አምላከ ዋልድባ ኢታርምም በክልኤ፡ወኢትጸመም ይእዜ፡
አምጣነ ጊዜነ ኮነ እንተ አራዊት ጊዜ።

ትርጉም:-

የዋልድባ አምላክ ሆይ በሁለት ነገር ዝም አትበል አሁንም ቸል አትበል፡
 ጊዜአችን የአውሬዎች ጊዜ ሆኗልና።

ርቃቄ ወይም ሐተታ፡

አንድ ሰው ተበድሎና በኃዘንና በመከራ ውስጥ ሲኖር ወደ  ፈጣሪው  በሁለት ነገር አትርሳኝ፤ዝም አትበለይ፤ ቸል አትበለኝ ጊዜአችን አውሬዎች የበዘቡት ጊዘ ነውና  ብሎ  ይጸልያል።እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት የምንገኝ ኢትዮ ጵያውያን ሁሉ በሀሀርችንም  በአንድነታችንም በሕዝባችንም ያለው ፈተና እያየን ወደ ፈጣሪ ስንጠይቅ ጽሎታችን ምርኩዛችን እርሱ ነውና ጥያቂአችን በሁለት ነገር ዝም አትበል ነው።

ቅኔ ማለት ምርምር ስለሆነ ሁላችንም ባለፉት ጊዜያት የዋልድባ አምላክ የሰራቸው ሁለት ነገሮችን አስበን ተመራምረን እንያቸው።
ጊዜአችን የአውሬ ጊዜ ሆኗልና  ማለት ቋንቋቸው፤ መልካቸው  በሰው አምሳል ባሕርያቸው ግን የአውሬ ባሕርይ የሆነ የበዙበት ሰዓት ነውና።
ጊዜአችን የአውሬ ጊዜ ሆኗልና ማለት በቤተ መንግሥቱ በቤተ ክህነቱም ያሉት እረኝነታቸውን ዘንግተው ለመንጋቸው እንደ አውሬ የሆኑበት ጊዜ ነውና።

2. ዘአምላኪየ :-
ኢትዮጵያ ኢትክሊ ቀዊመ ክልኤቲ አብራክ፡
እምእግርኪ እስከነ ኢወጽአ ኢህአዴግ ሶክ
ወይመልሖ አምላክ ለሕምዙ በመርፍአ ኃዘን ድሩክ

ትርጉም:-

ኢትዮጵያ ሆይ በሁለት እግርሽ መቆምን አትችይም፡
ኢህአዴግ እሾህ ከእግርሽ እስካልወጣ ድረስ፡
አምላክ ግን መርዙን(ሰንኮፉን) ጽኑዕ በሆነ ኃዘን መርፌ ነቅሎ ይጥለዋል።

3 ሚበዝኁ :-

ሐውልተ ኢያሱ ብሉይ ወሐውልተ ጴጥሮስ  አብ ሐዲስ በኀቤነ፡
እስመ ኢፍሉጣን ብሉይ ወሐዲስ መጻሕፍቲነ፡
ወእግዚአብሔር ሕያው ጸሐፈ ቦሙ ትዕዛዘ  ቃሉ እሙነ፡

ትርጉም:-

በእኛ ዘንድ የኢያሱ ሐውልት ብሉይ የጴጥሮስ   ሐውልት ሐዲስ ነው፡
ብሉይና ሐዲስ መጽሐፎቻችን አይለያዩምና፡
ሕያው እግዚአብሔርም የታመነ የቃሉን ትዕዛዝ ጽፎባቸዋልና።

4 ዋዜማ :-

ውሉድ ዘኢከረይነ
ወዘኢመላሕነ ቅድመ ለዕፀ መርገም ሥርዋ፡
ዕዳ ሔዋን ወዕዳ አዳም ተካፍልነ  ነዋ፡
እስመ ለዘሕይወት ምድር ኢትዮጵያ አጸዋ
ዘመከረ ብነ ምክረ አድዋ፡
ወአስሐታ ለእምነ ሸዋ።

ትርጉም:-

ጥንት የዕፀ መርገምን ሥር ያልነቀልንና ያልቆፈርን እኛ(ልጆች)፡
የአዳምና የሔዋን ዕዳን  እነሆ ተካፈልን፡
የአድዋ ምክር ዘረኝነትን የመከረብንና ሸዋ ሔዋንን ያሳታት  ከይሲ ወያኔ የሕይወት ምድር(ገነት) ኢትዮጵያን ዘግቶብናልና የአዳምና የሔዋን በደልም ተካፋዮች ሆንን።

5 ሥላሴ :-

ሕያው አምላከ ሙሴ፡
ለሊቃውንተ ጽድቅ ኅሩያኒከ፡
ሀበነ ኃይለ ሥጋዌ ወመንፈሳዌ ምናኔ፡
በሥጋነ ወበመንፈስነ ኢንርአይ   ኵነኔ፡
እስመ ሰዋቂነ እንተ ኲለሄ እምነ ጽኑዕ ትንታኔ፡
ወእንዘ ልቡሳን ኃይለ  ኵርጓኔ፡
ለዘዓመፃ ምሉዕ ቤተ ወያኔ፡
ናውዕዮ በእሳት ቅኔ።

ትርጉም:-

ሕያው የሆንክ የሙሴ አምላክ ሆይ፡
ለመረጥከን የጽድቅ ሊቃውንት፡
ሥጋዊ ኃይልንና መንፈሳዊ ምናኔ አድለን፡
በነፍሳችንም በሥጋችንም መጥፎ አገዛዝን እንዳናይ አድለን፡
አንተ ሁልጊዜ ጽኑዕ ከሆነ አወዳደቅ ደጋፊያችን ነህና፡
የአንድነት ኃይልንም ለብሰን አመፅ  የመላበት የወያኔ ቤትን በእሳት ቅኔ እናቃጥለዋለን(እናነደዋለን)።

6 ሣህልከ :-

ምኒልክ አልብከ ሕዝበ  ትርጓሜ፡
እስመ እንዘ ልኂቅ  አንተ እምኑኀ ዘመን ወዕድሜ፡
በውስጥ ወበአፍኣ ተደለዉ ከመ ይቅትሉከ ውሉዳ ለሮሜ፡

ትርጉም:-

ምኒልክ ሆይ የተግባር ሕዝብ የለህም፡
ከዘመንና ዕድሜ ብዛት የተነሳ አንተ ስትሸመግል (ስታረጅ)
በውስጥም በውጭም
ሊወጉህ(ሊያጠፋ) ሮማውያን ተዘጋጅተዋልና።

7 መወድስ  :-

ነገረነ ጴጥሮስ ከመ ንለብዎ
ለዘነገረነ ጴጥሮስ በሕያው ቃለ መልእክቱ፡
እስመ ከመ ሕስው ሕልም ወከመ ጽላሎት ከንቱ፡
ዓለመ ጥፍአት ወሙስና፡
ኢህአዴግ ወዘኢህአዴግ  ኃላፌ ውእቱ፡
ወእግዚአብሔር ያለብሶሙ፡
ለአርክቲሁ ትፍሥሕተ ወኀፍረተ ለጸላእቱ።

ለዓለም :-

እመ ኮነሂ በኵረ ሠረቀት ወቀተልተ  ነፍስ እምጥንቱ፡
ምንት ለዘአመፃ መንግሥተ  ኢህአዴግ በቊዔቱ፡
አምጣነ  ጽሉአን በሕዝብ ወእግዚአብሔር ክልኤቱ፡
ኢህአዴግ ቀታሌ ነፍስ ወቀታሌ ፍትሕ ሕገ መንግሥቱ።

ትርጉም:-

ሐዋርያው ጴጥሮስ ሕያው በሆነ ቃለ መልእክቱ የነገረንን(ያስተማረንን) እንድናስተውለው ኢትዮጵያዊው ሰማዕቱ ጴጥሮስ ነገረን፡
እንደ ሐሰተኛ ሕልምና እንደ ከንቱ ጥላ( ጥላ ሞት)፡
የጥፋትና የሙስና ዓለም ኢህአዴኤግ ኃላፊ: ምኞቱም ኃላፊ ነውና፡
እግዚአብሔርም ለወዳጆቹ ደስታን: ለጠላቶቹም ኃፍረትን ያለብሳቸዋልና።


ከጥንት(ከመነሻው) ጀምሮ የሌቦችና የነፍስ ገዳዮች አለቃ(መሪ) ከሆነ፡
አመፃ  የመላበት የኢህአዴግ መንግሥት ጥቅሙ ምንድን ነው(ነበር)?
ነፍሰ ገዳይ ኢህአዴግ ፍትሕ ገዳይ ሕገ መንግሥቱ  በእግዚአብሔርና በሕዝብ ዘንድ የተጠሉ ናቸውና።


8 መወድስ:-

ሰቆቃወ ራሔል ስምዕ ለእለ ናስቆቁ፡
ወንበኪ ሕዝብ ኢንኅድግ ብካየነ፡
እስመ እመ በጾም ባቊዕ ወበአስቆቅዎ ነበርነ፡
ይበትክ መሥገርተ ወያኔ(ወናመስጥ) (ወንድኅን) ንሕነ፡
ወአምላከ ሰላም ኢይጐነዲ
ማዕሠረ ጸላዒ ወፀር ይብትክ (ያሰሰል) እምኔነ።

ለዓለም:-

እምትካትሂ አመ ሀሎ እግዚአብሔር ምስሌነ፡
ኢተሀየሉነ ሰብአ ግብፅ ወሰብአ ሮሜ  ኢያፍርሁነ፡
አምጣነ ሃይማኖት በምንት ኢይሌልየነ፡
ወእግዚአብሔር ዘየአቅባ ለኢትዮጵያ ይረድአነ።


ትርጉም:-

ከጥንት አንስቶ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በነበረ ጊዜ፡
የግብፅ ሰዎች አልተበረታቱብንም ሮማውያንም አላስፈሩንም፡
ሃይማኖት በምንም አየለየንምና፡
ኢትዮጵያን የሚጠብቃት እግዚአብሔርም ይረዳናልና።

ፈፅመን ለምናለቅስ ለእኛ ኃዘናችንን(ልቅሶአችንን) እንዳንተው የራሄል እንባ አብነት (ምስክር) ነው፡
ጠቃሚ በሆነ ጾምና ልቅሶ ከኖርን (ከተወሰንን)፡
የወያኔ ወጥመድ ይቆረጣል እኛም እንድናለንና፡
የሰላም አምላክም የጠላት ወጥመድን ማሠሪያ ከእኛ ይቆርጥ (ያስወግድ) ዘንድ አይዘገይምና።


አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈፀመን ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋን ይግባውና  በሚቀጥለው ዓምዳችን የቀሩትን ማለትም ሳይብራሩ የቀሩት ቅኔያት አብራርተን : እንዲሁም አዲስ ቅኔያትም ጨምረን ይዘን እንቀርባለን።እስከዚያው አምላከ ሰላም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን: ለቤተ ክርስቲያችን አንድነትን: ለአጥፊዎች ልቦናን: የአውሬ ባሕርይ ላላቸው የሰው ባሕርይን: እንዲመልስልን ከልብ እንመኛለን።
ይቆየን!
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን::